የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የማኅበረሰብ ጤና መድኅን የንቅናቄ መድረክ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።በውይይቱ ላይ የተገኙ የወረዳ እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች የጤና መድኅን ሥርዓት በአጭር ጊዜ ታላቅ ለውጥ የተገኘበት ቢኾንም በክልሉ የተከሰተው አለመረጋጋት ለሥራው እንቅፋት መኾኑን ገልጸዋል። አሁንም በፀጥታ ችግር ውስጥ ያሉ አካባቢዎች በመኖራቸው ሥራውን በስኬታማነት ለመሥራት መቸገራቸውንም ተናግረዋል።
በቀሪ ጊዜያት የተፈጠሩትን ክፍተቶች በመሙላት እቅዳቸውን ለማሳካት እንደሚሠሩም አመላክተዋል። ማኅበረሰቡ የጤና መድኅን አገልግሎት ጥቅምን በሚገባ መረዳቱንም ገልጸዋል። የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ችግር መኖር እየፈተናቸው መኾኑንም ተናግረዋል።
ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የጤና አገልግሎት ችግር መግጠሙንም አንስተዋል። ዓመታዊ መዋጮ መሸፈን ለማይችሉ ወገኖች ልዩ ትኩረት መስጠት እና ዝቅተኛ የወር ደመወዝ ተከፋይ የኾኑ ዜጎችን የጤና መድኅን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
የኑሮ ውድነቱ የበደለውን ማኅበረሰብ ከጤና መድኅን ውጭ ታከም ማለት ከባድ ውሳኔ መኾኑንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ በአማራ ክልል የጤና መድኅን ተጠቃሚ ከኾኑ ወረዳዎች መካከል 40 የሚኾኑት በዘንድሮው ዓመት ወደ ሥራ አለመግባታቸውን አመላክተዋል። አንዳንድ ዞኖች ምንም ዓይነት የንቅናቄ መድረክ አለማካሄዳቸውንም አስታውቀዋል።
የጤና መድኅን ሥራን መሪዎች በዘመቻ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል። በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በርካታ እናቶች ቤት ውስጥ እየወለዱ እና በርካታ ሕጻናት ክትባት አለመጀመራቸውንም አስታውቀዋል። ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የጤናውን ዘርፍ የሚመሩ መሪዎች ብቻ ሳይኾን ሌሎች መሪዎችም ለጤና መድኅን ሥራ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት።
የመድኃኒት እጥረትን ለመፍታት የከተማ መድኃኒት ቤቶችን ማቋቋም እንደሚገባም አመላክተዋል። ለመድኃኒት የተበጀተውን በጀት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል። የጤና መድኅን ሥራ የመሪዎችን ትኩረት እንደሚጠይቅም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ወርቁ ዜጎች ለጤና ችግር ከመጋለጣቸው በፊት ለጤና መድኅን መዋጮ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ሥራውንም በተነሳሽነት እና በቁርጠኝነት መሥራትን ይጠይቃል ነው ያሉት።
ሕዝብ በቂ የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳለው የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ መሪዎች ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራውን በአግባቡ በመምራት ለሕዝብ በቂ የጤና አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።