በአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና በአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ትብብር በባሕር ዳር ከተማ የተገነባው የሴቶች የጉዳት ማገገሚያ ማዕከል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጌጎ ተስፋዬ (ዶ.ር) ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥት ለዜጎች ቅድሚያ በመስጠት ሰው ተኮር ሥራዎች ላይ ርብርብ ሲያደረግ ቆይቷል ብለዋል። ከእነዚህ መካከልም የተቋም ግንባታ አንዱ መኾኑን አንስተዋል።
ከተባበርን እና በተቋም ሳንታጠር በጋራ ከሠራን ሀገርን እና ሕዝብን የሚጠቅም ለትውልድ የሚሻገር ተግባር ማከናወን እንችላለን ነው ያሉት። የተገነባው የሴቶች ማገገሚያ ማዕከል አንዱ የትብብር ማሳያ ነው ብለዋል።
ተቋማት ተገንብተው የሚቆሙ ሳይኾኑ ዘላቂ አገልግሎትን ለማኅበረሰቡ በውጤታማነት መሥጠት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል። ወደ አገልግሎቱ ለማስገባት በሚደረገው ሂደትም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) አሁን ላይ በክልሉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች በዘላቂነት እንዳይከሰቱ በሰው አዕምሮ ላይ በመሥራት አስተሳሰብን መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል።
የተገነባው ማዕከል ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች ከአካላዊ ጉዳት ባለፈ የስነ ልቦና ድጋፍ የሚደረግበት በመኾኑ ከየትኛውም ተቋም በላይ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል። ማዕከሉን በመገንባት ትብብር ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የጤና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ “ጤና ለሁሉም” በሚል መሪ መልዕክት በመነሳት የአካል እና የስነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸውን አካላት በማካተት ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት የምንሰጥበት ነው ብለዋል።
ማዕከሉ ለክልሉ ማኅበረሰብ ፋይዳው የጎላ መኾኑንም አንስተዋል። በቀጣይ ሥራውን ለማስጀመርም ከጤና ጋር ተያያዥ የኾኑ ቁሳቁሶችንም በማሟላት በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሴቶች የበርካታ ጉዳቶች ሰለባ ኾነዋል ነው ያሉት። በክልሉ በተለያዩ ዞኖች ባሉ የጤና ተቋማት 17 ማዕከላት መኖራቸውን አንስተዋል። እያጋጠመ ያለውን ጉዳት መነሻ በማድረግም በክልል ደረጃ የማገገሚያ ማዕከሉን መገንባት ማስፈለጉን አንስተዋል።
ማዕከሉ በተለይም በጦርነት እና በግጭት ምክንያት ሴቶች ከደርሰባቸው የአካላዊ እና የስነ ልቦና ጉዳቶችን የሚያገግሙበት ነው ብለዋል። ወደ ሥራ ለማስገባትም ተቋም ኾኖ የሚቀጥልበት ደንብ ተዘጋጅቶለታል ነው ያሉት።
በቀጣይም በአጭር ጊዜ አገልግሎቱን ለማስጀመር የአጋር አካላትን ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት። 36 ክፍሎች ያሉት ማዕከሉ ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት መኾኑንም በምረቃው ወቅት ተገልጿል።