የጡት ካንሰር ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ምክንያቶች

– እድሜ

አብዛኛዎቹ የጡት ካንሰሮች ከ35 ዓመት በኋላ ይከሰታሉ።

– የጄኔቲክ ሚውቴሽን፦ እንደ BRCA1 እና BRCA2 ባሉ አንዳንድ ጂኖች ላይ የተደረጉ ለውጦች (ሚውቴሽን) ያላቸው ሴቶች ለጡት እና ኦቫርይ ካንሰር ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው።

– የመራቢያ ታሪክ

የወር አበባ ጊዜያትን ከ 12 አመት በፊት መጀመር እና ከ 55 አመት በኋላ ዘግይቶ መቆም ሴቶችን ረዘም ላለ ጊዜ ለሆርሞን ያጋልጣል, ይህም በጡት ካንሰር የመያዝ እድላቸውን ከፍ ያደርገዋል።

– የጡት ካንሰር የግል ታሪክ ወይም አንዳንድ ካንሰር ያልሆኑ የጡት በሽታዎች።

– የጡት ወይም የማህፀን ካንሰር የቤተሰብ ታሪክ።

አንዲት ሴት እናት፣ እህት ወይም ሴት ልጅ (የመጀመሪያ ደረጃ ዘመድ) ከእናቷ ወይም ከአባቷ ወገን የጡት ወይም የማህፀን ካንሰር ካለባት ለጡት ካንሰር የመጋለጥ እድሏ ከፍ ያለ ነው።

– የጨረር ሕክምናን በመጠቀም ያለፈ ሕክምና።

ከ30 ዓመታቸው በፊት በደረት ወይም በጡት ላይ የጨረር ሕክምና የወሰዱ ሴቶች በኋለኛው ሕይወታቸው በጡት ካንሰር የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

– አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ፤

– ከመጠን በላይ መወፈር፤

– ሆርሞኖችን መውሰድ፦ በማረጥ ወቅት የሚወሰዱ አንዳንድ የሆርሞን ምትክ ሕክምና ከአምስት ዓመት በላይ ሲወሰዱ ለጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ሊጨምሩ ይችላሉ።

– የእርግዝና ታሪክ

ከ30 ዓመት በኋላ የመጀመሪያ እርግዝና መኖሩ፣ ጡት አለማጥባት እና መካን መሆን የጡት ካንሰርን ተጋላጭነት ሊጨምር ይችላል።

– አልኮል መጠጣት

የራስን ጡት በራስ የመመርመር ዘዴ

በወር አበባ ዑደት ምክንያት የሚመጣውን የጡት ቅርፅ, መጠንና ስሜት ለውጥ ለመቀነስ በየ ወሩ በተመሳሳይ ጊዜ የወር አበባ በመጣ ከ 1 ሳምንት በኋላ የሚደረግ ሲሆን፤

– በመስተዋት ፊት በመቆም ከወገብ በላይ በማውለቅ እጅን ጎን ላይ በማድረግና ቀጥ ብሎ በመቆም በሁለቱም ጡቶች ላይ ያሉትን ለውጦች ማስተዋል። የጡቶቹ ጫፍ የሰረጎዱ፣ በተለየ መልኩ የቀሉ፣ ሁለቱ ጡቶች ካላቸው የተፈጥሮ ልዩነት በስተቀር ሌላ የመጠንም ሆነ የቅርፅ ልዩነትና የጓጎለ እብጠት እንዳላቸው ማየት

– ሁለቱንም እጆች ከጭንቅላት ትክክል ከፍ አድርጎ በመያዝ ከላይ የተዘረዘሩት አይነት ለውጦች ካሉ ማስተዋል

– አንደኛውን እጅ ከጭንቅላት በላይ ከፍ በማድረግና በሌላኛው እጅ ደግሞ በተቃራኒው ያለውን ጡት በመዳሰስ እብጠት ወይም ለየት ያለ ነገር መኖሩን ማረጋገጥ

– በጀርባ በመተኛት አንደኛውን እጅ በመንተራስ በሌላኛው እጅ በተቃራኒው ያለውን ጡት ዙሪያውን ቀስ እያሉ መዳበስ በመጨረሻም ወደ ብብት ውስጥ የሚሄደውን የጡት ስር በመዳሰስ የጓጎለ ነገር ወይንም እብጠት መኖሩን መመርመር

– የጡቶችን ጫፍ በማለብ ደም ወይንም ያልተጠበቀ ፈሳሽ መኖሩን ማየት ይገባል።

ምንጭ፦ ዶ/ር ተመስገን ሹሜ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ሀኪም ከሰጡት ምክር የተቀነጨበ

Get 30% off your first purchase

X