ፕሮግራሙን ከጤና ኤክስቴንሽን ጋር በማስተሳሰር የዘመነ የክትባት ክፍል መፍጠር ይገባል፦ ገስጥ ጥላሁን
ሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ከህፃናት አድን ድርጅት ጋር በመሆን በክትባት አገልግሎት ዙሪያ የተሟጋች ቡድን ዉይይት አካሄደ።
ሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ እና ህፃናት አድን ድርጅት በጋራ በመሆን ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች ፣ ከአጋር ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ከሚመለከታቸዉ ባለሞያዎች ጋር በመሆን ህፃናት አድን ድርጅት በሚሰራባቸዉ ዋድላ እና አንጎት ወረዳዎች የክትባት አፈፃፀም እንዲሻሻል የተሟጋች ቡድን ዉይይት አካሂደዋል።
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሐላፊ አቶ ገስጥ ጥላሁን ፕሮግራሙን ከጤና ኤክስቴንሽን ጋር በማስተሳሰር የዘመነ የክትባት ክፍል እና የተሻሻለ የክትባት ግብአት አያያዝ ስርዓት መፍጠር ይገባል ብለዋል።
ሃላፊው አያይዘውም ፕሮግራሙ የክትባት አገልግሎቱን ከሌሎች የጤና ስራዎች ጋር በማስተሳሰር አቅምን አሟጦ በሀብትም በሀሳብም መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
የጤና ትምህርት እና ተግባቦት ስራዉ ተሳፊዎችን እና ታላሚዎችን መሰረት በማድረግ የጤና ንቃተ ህሊና ያደገ ማህበረሰብ መፍጠር ይገባል ያሉት አቶ ገስጥ የምንፈልገዉን የጤና ስርአት ለመፍጠር በተግባቦት ስራ ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ ሲ/ር ፈለቁ መኮነን በበኩላቸው ሁለቱ ወረዳዎች በተለየ መልኩ በዚህ ፕሮጀክት እየተደገፉ የልህቀት ማዕከል በመሆን የሌሎች ወረዳዎች የልምድ መቀመሪያ ሆነዉ ማገልገል አለባቸዉ ሲሉ ገልጸዋል።
ወረዳዎቹ በፕሮጀክቱ ካልታቀፉ ወረዳዎች በተሻለ መፈፀም አለባቸዉ ያሉት ሲ/ር ፈለቁ በተለይ ለክትባት ቤተሰቦች አመች የሆነ ማህበረሰቡ የሚገለገሉበት የክትባት ክፍል እና ጤና ተቋም መፍጠር እንደሚገባ ገልፀዋል።