፦ አበበ ተምትሜ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የድጋፍ ቡድን አባላት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ በመገኘት የአካል ድጋፍ አደረጉ። ድጋፍ እና ክትትሉ በበጀት ዓመቱ በጎንደር ክላስተር በሚገኙ ልዩ ልዩ የጤና ተቋማት የተመዘገቡ ውጤቶችን እና የታዩ ጉድለቶችን በመለየት የክልሉን ህዝብ በጤናው ዘርፍ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ የድጋፍ ቡድኑ በበጀት ዓመቱ በዞኑ እየተከናወኑ የሚገኙ የጤና ልማት ስራዎች አፈጻጸሞችን መገምገምና የቀጣይ ወራት ተግባራትን መደገፍ ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል። የድጋፍ ቡድኑን የመሩት በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ ዞኑ በበጀት ዓመቱ ያከናወናቸውን መልካም ተግባራት አድንቀው በቀሪ ወራት በትኩረት ሊሰሩ የሚገባቸውን ተግባራት ጠቁመዋል። መምሪያው በዋናነት ካለፈው ዓመት ትምህርት በመውሰድ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ላይ በትኩረት በመስራት ውጤት ማስመዝገብ እንዳለበት አንስተው የድጋፍ ቡድኑ ዓላማም ይህንኑ ለመደገፍ መሆኑን ገልጸዋል። ኢኒሼቲቮችን በልዩ ቅንጅነትና ቁርጠኝነት መምራት እንደሚገባ ያሳሰቡት ሃላፊው ሁሉንተናዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል። አመራሩና ባለሙያው የጤና ዕቅዱን ለማሳካት ሙሉ ጊዜውን በስራው ላይ ማዋል አለበት ያሉት አቶ አበበ አገልግሎት ፈላጊውን ማህበረሰብ ማርካት የሚቻለው ባለሙያው በሚሰጠው ቀልጣፋ አገልግሎት መሆኑን ተናግረዋል። በውይይት መድረኩ በዝቅተኛ ደረጃ የተፈፀሙ ተግባራትን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይቱ ተጠናቋል። የድጋፍ ቡድኑ በጎንደር ክላስተር ( ጎንደር ከተማ አስተዳደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ምዕራብ ጎንደር ዞን፣ ሰሜን ጎንደርና እና ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን) ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ በመገኘት ድጋፉን ጀምሯል። ድጋፍ እና ክትትሉ ለተከታታይ አስራ አምስት ቀናት የጤና መምሪያው ጨምሮ እስከ ወረዳ ድረስ በመውረድ በሆስፒታሎች እና በጤና ጣቢያዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል።