የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የመረጃ እና የጤና ዲጅታል ሳምንት

በጤና ተቋማት የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት በማዘመን ጥራቱን የጠበቀና ቀልጣፋ አገልግሎት ማህበረሰቡ እንዲያገኝ በትኩረት እየተሰራ ነው:- አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የመረጃ እና የጤና ዲጅታል ሳምንት “በጤና መረጃ እና ዲጅታል ጤና ፈጠራዎች ላይ ዘላቂ ኢንቨስትመንት በማድረግ የጤና ቱርፋቶችን ማሳደግ” በሚል መሪ ሀሳብ በባህር ዳር ከተማ ተከበረ።

በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ እንደገለጹት ጥራት ያለው የጤና መረጃ ለጤናው ዘርፍ ከሀብትነቱ ባለፈ ህይዎት ነው ብለዋል።

መረጃን ሰብስቦ፣ተንትኖና አደራጅቶ ለውሳኔ መጠቀም በጤና ተቋማት የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀና ቀልጣፋ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል።

የጤና መረጃ ስርዓቱንና ጤና ዲጅታል ማጠናከር ላይ ትኩረት ተሰጦ በተሰራው ስራ ተቋማት ከወረቀት ነጻ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አሳውቀዋል።

የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ለውሳኔ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች በጤና መረጃ እና ዲጅታል ጤና ፈጠራዎች ላይ ዘላቂ ኢንቨስትመንት በማድረግ የማህበረሰቡ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።

በመረጃ አብዩት የተሻለ የፈጸሙ የከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያዎች፣የወረዳ ጤና ጽ/ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች እውቅና ተሰጧል።

በመድረኩ የቢሮ አመራሮችና የማኔጅመንት አባላት፣ከአማራ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፣የሁሉም ዞንና ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው ባለሙያዎችና አጋር አካላት ተገኝተዋል።

Get 30% off your first purchase

X