በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር በከሚሴ ከተማ በመልሶ ማቋቋም የተገነባው የጤና ተቋም ግንባታው ተጠናቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ኡስማን አሊ፦ ማህበረሰቡ የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኝ ጤና ኬላዎችን የማሳደግ ስራዎች እየተሰራ ይገኛል። በዚህም ማህበረሰቡ ጤና ተቋማትን በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ እና እንግልት እንዳይደርስበት ታሳቢ ያደረገ የጤና ተቋም ግንባታ ሲሆን በቀጣይ በጤና ተቋሙ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን ሙሉ የማድረግ ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ጤና ተቋሙ አክሞ የማዳንና ቀድሞ የመከላከል ፖሊሲን አንግቦ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፦ በዚህም የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ እና ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ማህበረሰቡ በራሱ ጤና ላይ ባለቤት ሊሆን ይገባል በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን መመሪያ መተግበር ይገባል ብለዋል።
ማህበረሰቡ የሚገነቡ ጤና ተቋማትን በባለቤትነት ሊጠብቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የከሚሴ ከተማ ምክትል ከንቲባና ስራና ስልጠና ፅ/ቤት ሀላፊ አረቡ አሊ በበኩላቸው፦ መሰረታዊ የጤና ኬላ አገልግሎትን ለመስጠት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር የጤና ተቋሙ ሲሆን የበለጠ እያደገ የሚሄድበት እና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግበት የጤና ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
ለአካባቢው ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ማህበረሰቡ የጤና አገልግሎትን በቅርበት ለማገኘት አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር ታሳቢ አድርጎ የተገነባ ጤና ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል።
በጤና ተቋሙ አገልግሎት እያገኙ የሚገኙ የከሚሴ ከተማ ቃጩር ቀበሌ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፦ ጤና ተቋሙ በአካባቢያቸው በቅርበት አገልግሎት መስጠት መቻሉ እንዳስደሰታቸው ገልፀው በቀጣይ በጤና ተቋሙ አስፈላጊ የህክምና መሳሪያዎችን ማሟላት ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
እንደ ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ኮሙኒኬሽን መረጃ የከሚሴ ከተማ ቃጩር ቀበሌ ጤና ተቋም ግንባታ በመልሶ ማቋቋም ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተገነባ በመርሐግብሩ ተገልጿል።