ወረዳው ለጤና መድህን ሽፋን በልዩ ክትትል መስራት አለበት

የጎንደር ክላስተር የድጋፍ ቡድን በአዲ-አርቃይ ወረዳ ባደረገው ድጋፋዊ ጉብኝት የታዩ አፈጻጸሞችን መነሻ ያደረ ግብረ መልስ ለወረዳው አስተዳደር ሰጧል።

‎‎የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ ጤና ጣቢያው የእናቶችንና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት መስራት እንዳለበት ጠቅሰው ከቅድመ ወሊድ እስከ ድህረ ወሊድ ድረስ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

‎‎ጤና ጣቢያው ትንሽ ድጋፍ ቢደረግለት ሞዴል መሆን የሚችል ነው ያሉት አቶ አበበ ጤና ጣቢያው ያሉበትን ጉድለቶች በማረም እናቶች ላይ ሊደርስ ከሚችል አላስፈላጊ እንግልት ማዳን ይገባል ብለዋል።

‎‎በጤናው ዘርፍ ቀበሌዎችን ሞዴል በማድረግ ጤናማ አከባቢን ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደለበት የገለጹት ሃላፊው ውጤታማ ስራ መስራት የሚቻለው አጠቃላይ ማህበረሰቡን ባለቤት አድርጎ በማሳተፍ መሆኑን አመላክተዋል።

‎‎የጤና መድህን አገልግሎት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን ከከፋ ህመምና ሞት የሚታደግ የህክምና ስርዓት ነው ያሉት አቶ አበበ የወረዳው አመራር በልዩ ትኩረት ሊመራውና ሊከታተለው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

‎‎የትኛውም የልማት ስራ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ መገንባት ሲቻል ነው ያሉት ሀላፊው ዜጎች ለሚያጋጥማቸው ድንገተኛ የጤና እክል ከጤና ጣቢያ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ሆስፒታሎች ሕክምና እንዲያገኙ መደረጉ ትልቅ ዕድል በመሆኑ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የጤና መድህን ተጠቃሚ እንዲሆን መስራት ይገባል ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል።

‎‎የአዲ-አርቃይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ አባተ በበኩላቸው በድጋፍ ቡድኑ የታዩ ግኝቶችን ለማስተካከል እንደሚሰራ ገልጸው ጤና ጣቢያው ለማህበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

‎‎ጤና ጣቢያው የነበረበትን የአምቡላንስ ችግር ተቀርፎለታል ያሉት የአዲ-አርቃይ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሳምሶን በቀለ ከክልሉ ጤና ቢሮ ሁለት አምቡላንሶችን በድጋፍ ማግኘታቸውን ተናግረው በአገልግሎት አሰጣጥ ህሙማንን ለማርካት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

‎‎ባለሙያዎች መልካም ስነ ምግባርን በመላበሰ በጥራትና በፍጥነት ለህሙማን አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ የጠቀሱት ኃላፊው ተቋሙ የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ችግር ለመፍታት እየሰራ ነውም ብለዋል።

Get 30% off your first purchase

X