የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ከዞን ጤና መምሪያ ኃላፊዎች ጋር ገመገመ
በግምገማ መድረኩ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ በችግር ውስጥ ሆነን የማህበረሰባችን ጤና እንዲጠበቅ የተሰሩ ስራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል።
የጤና ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት እንዳይስተጓጎል ተቋማቱ በመድሀኒት፣በህክምና መሳሪያዎችና በግብዓት እንዲሟሉ ትኩረት ተሰጦ እንደተሰራ ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።
በጸጥታ ችግር በአንዳንድ አካባቢዎች አገልግሎት ያቋረጡ ተቋማት ፈጥነው አገልግሎት እንዲጀምሩ አመራሩና ባለሙያው ላደረገው ርብርብ ምስጋና ያቀረቡት አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ፍትሀዊና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በግማሽ ዓመቱ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል ለነበሩ ክፍተቶች የጋራ መፍትሄ ሀሳብ በማስቀመጥ በቀሪ ወራት የታቀዱ ዕቅዶች ስኬታማ እንዲሆኑ አዳዲስ አሰራሮች በመተግበር በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅ ቢሮ ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።
በመድረኩ የ2016 በጀት ዓመት የ6 ወር አፈጻጸም፣ የድጋፍ ጉብኝት ሪፖርትና ሌሎች የውይይት መነሻ ሰነዶች ቀርበዋል።