አንድ ሰው የደም ማነስ ህመም አለበት የሚባለው በአንድ ወይም ከአንድ በላይ በሆኑ ምክንያቶች በደም ውስጥ የቀይ ደም ህዋሳት ቁጥር ሲመናመን ነው።የነዚህ ቀይ ደም ህዋሳት ተግባር በባለፈው ‘ቀዩ ቦርሳ’ በተሰኘው ጽሁፍ እንደተወሳው አየር መሸከም ሲሆን ቁጥራቸው በሚመናመንበት ጊዜ ከዚሁ ተግባር መስተጓጎል ጋር የተያያዘ ስሜቶችና (symptoms) ምልክቶች (signs) ይታያሉ።
ምልክቶች
▹ማዞር
▹ጆሮ ውስጥ ጭውው የሚል ድምጽ መሰማት
▹ብዥ ማለትና አንድ ነገር ሁለት መስሎ መታየት
▹የልብ ምት መሰማት እና የመሳሰሉት ሲሆኑ
የደም ማነሱ የከፋ ሲሆን ደግሞ ትንፋሽ ማጠርና ቶሎ ቶሎ መተንፈስ፣ የደረት ውጋትና የእግር ማበጥ ሊከሰት ይችላል።
ሃኪሞች በሚመረምሩበት ወቅት ደግሞ የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያስተውሉ ይችላሉ።
▹የፊትና የአይን ቆብ ውስጠኛው ክፍል መገርጣት/መንጣት
▹የምላስ ልሙጥ መሆን ወይም ስጋ መምሰል
▹የአፍ ጠርዝና የከንፈር ቁስለት
▹የመዳፍና የውስጥ እግር መንጣት/መገርጣት እና ወዘተ ሲሆኑ በተጨማሪም ለደም ማነሱ መንስኤ የሆኑ ሌሎች የውስጥ ደዌ ምልክቶችም ሊታዩ ይችላሉ።
ስለምን እኒህ የቀይ ደም ህዋሳት ቁጥራቸው ይመናመናል?
በአጠቃላይ የደም ማነስ ምክንያቶችን በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ማየት ይቻላል
1. ከሰውነት ደም መፍሰስ፣
በአደጋ፣ በወሊድ ጊዜ፣ የወር አበባ ከተለመደው ሲበዛ፣ በቀዶ ህክምና ወቅት፣ ከጨጓራና ከተለያዩ የውስጥ ኣንጀት ቁስሎችና እባጮች መድማትና ወዘተ
2. የቀይ ደም ህዋሳት ቁጥር ማነስ
-በበቂ ቁጥር ያለመመረት (የመቅኒ መስተጓጎል፣የብረት iron ቫይታሚን ቢ 12 እና ፎሊክ ኣሲድ እጥረት)፤ የተፋጠነ የቀይ ደም ህዋሳት መሞት፣ ከብረት (iron) እጥረት፤
ከላይ ያሉት ስሜቶችና ምልክቶች በብዙ ህመሞች ላይ የሚስተዋል በመሆኑ ታማሚው በኣቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ሊያደርግ ይገባል።የጤና ባለሞያዎችም ምርመራዎችን በላቦራቶሪ እንደየአስፈላጊነታቸው ሊያዙ ይችላሉ።
መከላከያ መንገዶች
በብረት የበለጸጉ ( ጉበት፣ ቀይ ስጋ፣ ዓሣ፣ ባቄላ፣ አተር ፣ ጥቁር ቸኮሌት እና ሌሎች )፤ በቫይታሚን ቢ 12 (vitaminB12) የበለፀጉ ምግቦች ( ቀይስጋ፣ ዓሣ፣ዶሮ ፣ እንቁላል ፣ወተትና ሌሎችም )፤ በፎሊክ አሲድ (folic acid) የበለፀጉ ምግቦች (አረንጓዴ ኣትክልት፣ አትክል( ጎመን፣ ሰላጣ)፣ ጥራጥሬዎች (ባቄላ፣አተር፣ምስር)፣ ለውዝ፤ ፍራፍሬዎች(ብርቱካን፣ሙዝ፣ወይን፣አቮካዶ፣ፓፓያ፣ እንጆሪ )፣ ቀይ ሽንኩርት እና ሌሎች ) ምግቦችን በመመገብ በነዚህ ንጥረ ነገሮች እጥረት የሚከሰተው የደም ማነስ መከላከል ይቻላል።ይህንንም የተመጣጠኑ ምግቦችን በመመገብ መከላከል እንችላለን።
በተጨማሪም የሆድ ትላትሎችን የግልና የአካባቢ ንፅናችንን በመጠበቅ መከላከል እንችለላለን።
ከላይ እንደተጠቀሰው እነዚህን ስሜቶችና ምልክቶች ስናስተውል በአፋጣኝ ወደ ወደጤና ተቋም ማምራት ተገቢ ይሆናል።